Blogs

ስለ ኢህአፓ ከቆንጅት ብርሃን ጋር

photo_2018-07-27_13-11-45

ስለ ኢህአፓ በደሴት አበበ

ስለ ፓርቲው ልሰማ አልነበረም ስብሰባውን የሄድኩት ይልቅስ የስብሰባው መጥሪያ እንደገለጠው የሴቶች ተሳትፎ በፓርቲው ውስጥ ምን ይመስል ነበር የሚለውን ለማወቅ ፈልጌ እንጂ፡፡ ውይይቱ ላይ እንደተገለጸው ኢህአፓላይ የተጻፉ መጽሐፍት በአብዛኛው በወንዶች የተጻፉ በሴቶችም ሲጻፉ ስለወንዶች የተጻፉ ከመሆናቸው አንጻር የሷ ታሪክ በኢህአፓውስጥ ምን ይመስላል ሴት አባላት በአመራርነት ውክልና ነበራቸው ወይ ፓርቲው የሴቶችን ጥያቄ እንዴት አስተናግዷል ሴቶች ነበረባቸው የሚለውን ድርብ ጭቆና ማለትም የኢኮኖሚና የጾታ እንዴት ሊያነሳላቸው ታግሏል የሚለውን ለመስማት ጓጉቼ ነበር፡፡ የተነሱ ጥያቄዎች የነበረው ውይይትም ከሆነ አመት በፊት ገዜጣ ላይ በሰጠሽው ኢንተርቪው ላይ ኢህአፓ አልተሸነፈም ብለሻል እንዴት ነው…የዛኔ የተከተላችሁት መስመር ልክ ነበር ወይ……ያንን ትውልድ ለምን መድገም አልተቻለም ትያለሽ ወዘተርፈ በሚሉ በዛ ሰዓት ጭራሽ ኢንተረስት በማያረጉኝ ጉዳዮች 60 ፐርሰንት ጊዜው የሄደበት እኔም ትዕግስቴ እየሟጠጠ የመጣበት ሁናቴ ነበር፡፡ ኤጭ ውይይቱ ሃይጃክ ተደረገ ወዝ ዋት አይፌልት፡፡ በእርግጥ ስለምፈልገው ጉዳይ ጠይቄም ከተነሱ አንድ አንድጥያቄዎች በመነሳትም የሚከተሉትን ነጥቦች ሰምቻለሁ፡

  1. ሴቶች ፓርቲውን ለመቀላቀል ከፍተኛ ጫና ነበረባቸው በተለይም ካለባቸው የቤተሰብ ቁጥጥር የቤት ውስጥ የስራ ጫና አንጻር በፓርቲው ለመሳተፍ ብሎም አስተዋጽዎ ለማድረግ ድርብ ድርብርብ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረባቸው፡፡ ከተቀላቀሉ በኋላ ግን ከወንዶች እኩል በብዙ መስክ አፈጻጸም ከማሳየት አልፈው በተለይ ሚስጥር እስከሞት በመጠበቅ ከወንዶች በላይ ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚም እንደነበር
  2. የሴቶች ተሳትፎ በዝቅተኛ የፓርቲው እርከን ላይ የጎላ ቢሆንም የሃላፊነት ደረጃው ከፍ እያለ ሲመጣ ቁጥራቸው እየተመናመነ እንደሚመጣ ድርጅቱ በዕቡእ የሚንቀሳቀስ የነበረ እንደመሆኑም በቁጥር አንጻር ሁነኛ መረጃ ሊገኝ እንደማይችል
  3. ትግል ውስጥ ልዩ ድጋፍ የለም እኩል ግዳጅ ይሰጣል እኩል እንድትወጣ ይጠበቅባታል
  4. ሴቶች በደርግ ሲያዙም ከፍተኛ ግፍ ይሰራባቸው ነበር ከመገረፍ አልፈው ጡታቸው በጋዜጣ ተጠቅልሎ በእሳት የሚቃጠሉ በማህጸናቸው ብረት የተከተተባቸው በብዙ መከራ ያለፉ አባላት አሉ፡፡

ሆኖም ታሪካቸው አሁንም አልተጻፈም፡፡ ፓርቲው በነበረበት ጊዜም ወደ ሃላፊነት ደረጃ እንዲያድጉ በቂ ድጋፍ አልተደረገም ……ለዚህ ነው የጠየቅኩት ፓርቲው አላማውን ለማስፈጸም ሴቶችን መሳሪያ እድርጓል ብለሽ ታስቢያለሽ ወይ

ከፍተኛ ቅሬታን የፈጠረ ጥያቄ ነበር፡፡ በፍጹም……..በአላማው አምኜበት ማንም ሳይገፋኝ የተቀላቀልኩት ወጣትነቴን ያሳለፍኩበት ፓርቲ ነው፡፡ በጭራሽ መሳሪያ አልነበርንም፡፡ እኔ አንኳን መሳሪያ ሆነናል ብዬ አላምንም የተሸለ የሚያሳምነኝ መልስ ነበር፡፡ ባለመሆን እና ባለማመን መካከል ልዩነት አለ፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በወንዶች ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ (ውክልናው ከመቶ ከ30 ያነሰ ከሆነ እንደሙሉ ሊቆጠር ይችላል) የሚመራ ከሆነ የሴቶችን ነባራዊ ሁኔታ አገናዝቦ ለጥያቄያቸው መልስ የማይሰጥ ከሆነ ሴቶችን ጠቀመ ነው ተጠቀመ የሚባለው የሴቶች የትግል አጋርነት ከድል በኋላም ሆነ በትግል ውስጥ እውቅናና ስልጣን የማይሰጣቸው አካሄድ የተለመደ ነው ምናልባት ይሄንን ለመቅረፍ ሴቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የራሳቸው አጀንዳ ምላሽ ካላገኘ አባል ባይሆኑ አባል ከሆኑም ሌሎችን ሴቶች መደገፍ ወደ አመራር እንዲመጡ መታገል እንዳይመጡ ጫና የሚደረግባቸው ከሆነም አብሮ አድሞ ድምጽ መንፈግ ወዘተ ስትራቴጂዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዳይረሳ መፃፍ መፃፍ አሁንም መፃፍ አስፈላጊ ነው ….. ምናልባት የኢህአፓም የደርግም ግማሽ ለግማሽ አመራሮች ሴቶች ቢሆኑ ኖሮ በስንት ስስት ተወልዶ ያደገ አንድ ትውልድን የሚጨርሱ አሰቃቂ ውሳኔዎች አይወሰኑም ነበረ…..የመጠፋፋት ፖለቲካ እንዲህ ዘመን ተሻግሮ እሳቱ አይለበልበንም ነበር…..አይታወቅም…..ያልተሞከረ ነው የሚቆጨው፡፡ ለማንኛውም ለወደፊቱ የተወሰነ እንደሚነካን እያየን ውሳኔው ላይ አሻራችንን የምናሳርፍበትን መንገድ በዚህም በዚያም ብሎ አፈላልጎ ለመደመር መጣር ነው ………. ያለባለቤቱ አይነድም እሳቱ እንዲሉ አበው (በነገራችን ላይ አበው ሴት ናቸው ወንድ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *