በኢፌድሪ ጠቅላይ ምክር ቤት ለተሾሙ ሴት የካቢኔ አባላት ሴታዊት እንኳን ደስ ያላችሁ ትላለች! በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ ለሴቶች ነፃነትና እኩልነት በየዘርፋችሁ አጥብቃችሁ እንደምትሰሩ እንተማመናለን።

በ2013 የምርጫ ቅስቃሳ ወቅት ‘ጠይቂ’ በተሰኘ የማህበረሰባዊ የሚዲያ ዘመቻ ሴታዊት የሴት መራጮች ጥያቄዎችን ሰብስባ ነበር። ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም እነዚህን ጥያቄዎችን እና በኢ.ሴ.ማ.ቅ. የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ሴቶች ማኒፌስቶ ላይ የተቀመጡትንጥያቄዎች በመጨመር  ለአዲሱ የመንግስት አባላት ለማቅረብ ትወዳለች።

የሴቶች የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ፣ የሰላምና ደህንነት ጥያቄዎች የሰባዓዊ መብት ጉዳይ እንደመሆናቸው መጠን በመንግስት ምስረታና አስተዳደር ተጨማሪ ድርሻ ሊይዙ ይገባል። ለካቢኔ ከተቀመጡት ሴት ሚንስትሮች በተጨማሪ ሴቶች በመንግስት አስተዳደር ላይ ከቀበሌ አስተዳደር ጀምሮ እንዲሳተፉና የሴቶችን ጥያቄዎችም የፖሊሲ፣ የህግ፣ የማስፈፀሚያ ስልት፣ በጀትና መዋቅር መድቦ ምለሽ እንዲሰጣቸው አዲሱን መንግስት እንጠይቃለን።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚያመለክቱት ሴቶች እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ድርሻ የላቸውም። ይህንን ለመቅረፍ ምን ለመስራት አቅዳችኋል? 

የትምህርት ፖሊሲ የሴቶችን ውክልና እና ተሳትፎ በምን አይነት መልኩ ይመለከተዋል? ለምሳሌ ከአዎንታዊ አድሎ (Affirmative action) ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚደርሱ ጥቃቶች እና ከአካል ጉዳተኛ ሴት ተማሪዎች አንጻር ምን ይላል? 

የስራ አጥነት ችግር እና የአረብ ሃገራት ያሉ ሴቶች መብታቸው እንዲከበር ብሎም ከዚህ ሃገር ሲወጡ የሚጠብቃቸውን በአግባቡ እንዲያውቁ ምን ለማድረግ አቅደዋል?

የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እንዲሁም የአብዛኛው ህዝብ ጥያቄ ከሌሎች ግዜያት በተለየ መልኩ በትግራይ ክልል ባለው ጦርነትና ሌሎች ቦታዎች ባሉት ግጭቶች ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የሴቶችን መደፈር ለማስቆም እና እነዚህን ሴቶች መልሶ ለማቋቋም ምን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው?

በግጭቶች ላይ ሴቶች ከሚደርሱባቸው ፆታዊ ጥቃቶች፣ እና ከአካባቢያቸው በመፈናቀል መጠለያ ውስጥ ከሚደርሱባችሁ ጥቃቶች ለማቆም እንዲሁም መልሶ ለማቋቋም ምንድነው እቅዳችሁ? 

የፖሊሲ መሻሻል በተለይም በጾታዊ ጥቃት ላይና ሰላም ለማስፈን ጥረቶች ላይ የሴቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሂደት መሻሻል ያስፈልጋል።

የፍትህ ተደራሽነት በንብረት ክፍፍል ፣ በፍቺ፣ በመሬት ባለቤትነት እና ከጾታዊ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ ተጠቂዎች መረጃ የሚያቀርቡበት የህግ ሂደትና የጤና አገልግሎት ሁኔታ መሻሻል ይኖርበታል።

ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ለጾታዊ ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛ እንዳይጋለጡ፣ በትምህርትና ስራ ዘርፍ መድሎ እንዳይደርስባቸው ምን ስራዎች ለመስራት ወስናችኋል?

በገጠር አካባቢ ሴቶች በአየር ንብረትና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች ይኖራሉ። ማገዶን ወደ በኤሌክትሪክ ሃይል መተካት፣ ንፁህ የውሃና መጸዳጃ አገልግሎት ማቅረብ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ገቢና አኗኗር ለተናጋባቸው በአርሶአደርና አርብቶአደርነት የሚተዳደሩ ማህበረሰቦች ድጋፍ ለመስጠት ምን አቅዳችኋል?

በኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት፤ ጤናቸውና አኗኗራቸው ለተናጋ ሴቶች የተለየ ትኩረት ለማድረግ ምን ታስቧል?