በሴቶች ላይ የሚፈጸምን የአሲድ ጥቃት በመቃወም በሴቶች መብት ተሟጋች ማህበራትና ድርጅቶች የተሰጠ የጋራ የአቋም መግለጫ


ቀን: ጥር 25/2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ

በሀገራችን የተለያዩ የሰብዓዊ መብትና የሴቶች ተቋማት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለማስቀረት በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑይታወቃል። ሴቶች ለጠለፋ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ አሰገድዶ መደፈር፣ ድብደባ፣ ግድያ እና የሌሎችም ጾታዊ ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸው ግን አሁንም ቀጥሏል። ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ የአሲድ ጥቃት በተደጋጋሚ እየተፈጸመ የምናስተውለው በሴቶች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ የጾታዊ ጥቃት አይነት ሆኗል። በሀገራችን በዓመት ከ50 እስከ 70 በሚደርሱ ሴቶች ላይ ይህ ጥቃት እንደሚፈጸም መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህንን ጥቃት በመቃወም የተለያዩ የሴቶች መብት ተሟጋች ተቋማት የተለያዪ የህግ ማሻሻያ የውትወታ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ። ሆኖም ግን የአሲድ ጥቃት በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ መሆኑና ተመጣጣኝ እንዲሁም አግባብነት ያለው ምላሽ እየተሰጠ አለመሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢው አትኩሮት እና ፍትሃዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል የሚለውን
ለማሳሰብና ጥያቄያችንን ለማቅረብ ይህንን የጋራ አቋም መግለጫ አውጥተናል።

ይህ የአቋም መግለጫ በህዳር 10 ቀን 2015 ዓ. ም ከንብረት ማውደም እንዲሁም ተደጋጋሚ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በኋላ በትዳር አጋሯ የአሲድ ጥቃት የተፈጸመባትን እና በጳውሎስ እና አቤት የሚባሉ ሆስፒታሎች ህክምና እየተከታተለች የምትገኘውን እና ደህንነቷን ከግምት ውስጥ በማስገባት ስሟ ያልተገለጸውን እህታችንን መነሻ በማድረግ የአሲድ ጥቃት በመቃወም የተሰጠ ነው።

የአሲድ ጥቃት በሀገራችን በተደጋጋሚ እየተከሰተ የመጣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት መሆኑ አስደንጋጭና የማይካድ እውነት ነው። ወንጀሉ ከተራ አካላዊ ጥቃት (ጉዳት) የማስከተል ወንጀልነት በዘለለ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሆኑ በአብዛኛው በእህቶቻችን ላይ መፈጸሙ እሙን ያደርገዋል። በርካታ እህቶቻችን በዚህ ጥቃት ምክንያት ህይወታቸውን እና አካላቸውን ብሎም ህልም እና ማንነታቸውን ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ አጥተዋል፤ እያጡም ይገኛሉ። ከአሲድ ጥቃት ያገገሙ ሴቶች ቀጣይነት ባለው የአካል ጉዳትና የሥነ ልቦና ቀውስ ጋር በመሆን ህይወታቸውን ለመምራት ይገደዳሉ። የአሲድ ጥቃት እንደ ህንድ ባሉ አንዳንድ ሀገሮች እንደሆነው ሁሉ የከፋ ጉዳት በሀገራችን ከማድረሱ በፊት መገታት ያለበት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት፣ የመብት ተቋማትና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ይህንን አሰቃቂ ጥቃት ለማስቀረት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪያችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን። ስለሆነም የአሲድ ጥቃት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመሆኑ ባለፈ የሚያሰከትለው አካላዊ፣ ሰነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን በማስረገጥ የሚከተሉትን የጋራ አቋም መግለጫ እናስተላልፋለን፤

1ኛ) የፍትህ ሚኒስቴር የአሲድ ጥቃት ከአካላዊ ጥቃት በተጨማሪ ፆታዊ ጥቃት በመሆኑ በወንጀል ህጉ ውስጥ ራሱን በቻለ አንቀጽ እንዲሰፍር ሊያደርግ ይገባል፤
2ኛ) የጤና ሚኒስቴር የአሲድ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ከህክምናው ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎቶች መድሃኒቶችን ጨምሮ በነጻ እንዲያግኙ ህግ ማውጣት አለበት፤
3ኛ) ንግድ ሚኒስቴር እና ገቢዎች ሚኒስቴር የአሲድ አቅርቦት ላይ አስፈላጊ ደንብ በማርቀቅ በህጋዊ ፍቃድ ብቻ ሽያጭ የሚፈጸም እንዲሆንና ከታቀደለት አላማ አልፎ በእህቶቻችን ላይ ጥቃት መፈጸሚያ እንዳይሆን ክልከላ ሊያደርጉ ይገባል፤
4ኛ) ጤና ሚኒሰቴርና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሲድ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ተገቢውን የማገገሚያ፣ የስነ-ልቦና፣ የህክምና፣ የኢኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፤
5ኛ) ፍርድ ቤቶች ጥቃት አድራሾች ላይ ፈጣንና ተመጣጣኝ የህግ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፤
6ኛ) የጸጥታ አካላት ጾታዊ ጥቃቶችን የመከላከል ስራዎቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፤ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ጾታዊ ጥቃቶችን የመቃወም ባህሉን በማዳበር ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል።

ይህንን የጋራ የአቋም መግለጫ ያስተላለፍን የሴቶች መብት ተሟጋች ተቋማት ኃላፊነታችንን አጠናክረን የምንወጣ ሲሆን ይህ ጥሪ የደረሳችሁ ሁላችሁም በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለማስቀረት ለምታሳዩት አንድነትና ለምታደርጉት ትብብር እናመሰግናለን።

የዚህ የጋራ የአቋም መግለጫ ፈራሚዎች ከታች ያሉ ተቋማትና ማህበራት ናቸው።
1. ሴታዊት ንቅናቄ
2. ሲቄ ውመንስ ድቭሎፕመንት አሶሲዬሽን
3. የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት
4. አዲስ ፓወር ሀውስ
5. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል
6. የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር
7. ሴታሴት
8. የኢትዮጵያ ሴት ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥምረት

Privacy Preference Center