በእየሩሳሌም አስራት ላይ የደረሰውን ግድያ ዝም ብለን አናልፍም!

እየሩሳሌም አስራት በህዳር 13 ቀን 2016 በፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ጀርባዋ ላይ ተመትታ ከሶስት ቀናት በኋላ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ህይወቷ አልፏል። ጉዳዩን የዘገቡት አሃዱ ሬድዮ እና ቲክቫ ጥቃቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ቀበሌ 25 መሆኑንና ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ ገልጸዋል።
የሴቶች በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ጥቃቶች መጋለጥና ለህይወት ህልፈት መዳረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣ ድርጊት ሆኗል። በተለይም ደግሞ የህግ ማስፈጸም ሃላፊነት በተሰጠውና ለዜጎች ከለላ መስጠት በሚገባው የፖሊስ አባል ይህ ወንጀል በመፈጸሙ ከልብ ማዘናችንን እንገልጻለን።

በጸጥታ አባላት በማንአለብኝነት የሚገደሉ ሴቶችን አሳዛኝ ዜናዎች በተጋጋሚ እየሰማን መሆኑ አስደንጋጭና አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ይህ ወንጀል በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ የተፈጸመ ወንጀል አይደለም፤ ጉዳዩ የፖሊስን የህዝብ አገልጋይነት፣ ተዓማኝነት እና አጠቃላይ ምስል ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። በተጨማሪም የተፈጸመው ወንጀል የሴቶች ከጥቃት የመጠበቅና ከለላ የማግኘት የመብት ጥያቄዎችን ድርጊት የበለጠ ስጋት ውስጥ ያስገባ ነው።

የፌደራል ፖሊስና የጸጥታ አካላት አባላቶቻቸውን የመመልመልና የማሰልጠን ተግባራቸውን አንዲያጤኑ፤ በአባላቶቹ እና ተቋሙ ላይ ከባድ የፍተሻ፣ የምዘና፣ የቁጥጥርና የዲስፕሊን ማስተካካያ እርምጃ ሊያደርግ እንደሚገባ እየገለጽን ፤ ፖሊስ ተጠርጣሪው የፖሊስ አባል የፈጸመውን የወንጀል ድርጊት በህይወት የመኖር መሰረታዊ ህገመንግስታዊ መብትን ከመጣሱም በላይ ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ የወጡግ የህገመንግስቱን መርሆች እና ህግጋቶችን የፌደራል ፓሊስ አባላት ሚኒስቴር ካውንስል መተዳደሪያ ደንብ 260/2012፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 720/2011 እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አዋጅ 313/2003 እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ 86/2003ን የሚጣረስ ድርጊት በመሆኑ አጽንዖት በመስጠት ይህ የፖሊስ አባል ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለፍትህ ስርዓቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እና የፖሊስ ኮሚሽኑ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ያላሰለሰ እና ቀጣይነት ያለው ትብብር እንዲያደርግ እንዲሁም በአግባቡ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን፤ እናሳስባለን።

የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና የሴቶች መብቶች ተቋማት እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን በከፍተኛ ደረጃ እንዲመለከተው እና ማንም ሰው ፖሊስን ጨምሮ ከህግ በታች መሆኑኑን እንዲያረጋግጥና ለእየሩሳሌም አስከፊ ሞት ግልጽና ተገቢው የፍትህ ምላሽ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።

ፈራሚ ድርጅቶች
1. ሴታዊት ንቅናቄ
2. ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ ደቨሎፕመንት አሶሴሽን (ኤሊዳ)
3. አዲስ ፓወርሃውስ
4. ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጰያ
5. የኢትዮጵያ ሴት የህግ ባለሙያዎች ማህበር (EWLA) 
6. የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች (EWRA)
7. የኢትዮጵያ የመብት ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)Privacy Preference Center